Search

የራስ መከላከያ ቁሳቁስ (PPE) እጥረትና የኢትዮጵያ ጤና ባለሙያዎች እሮሮ

በአናቤል ሽመክት (@AnnabelLemma) እና ማስተዋል ታደሰ (@Mastishtt) | ሰኔ 5, 2012እስካለፈው የግንቦት ወር ድረስ በአለማችን ከ200,000 በላይ የሚሆኑ የጤና ሰራተኞች በኮቪድ19 በሽታ እንደተያዙ እንደሚገመት ሮይተርስ ጋዜጣ ዘግቧል። ይህ አሀዝ በሀገራት ተለይቶ ከኮቪድ 19 በሽተኞች ጋር በምጣኔ ሲቀመጥ አንዳንድ ሀገሮች የጤና ባለሙያዎቻቸውን ከሌሎች ሀገሮች በተሻለ ሁኔታ ከለላ እና ጥበቃ እንዳደረጉላቸው ያሳያል። በአሜሪካ ብቻ 75, 763 የጤና ባለሙያዎች በበበሽታው የተያዙ ሲሆን 409 የሚሆኑት ህይወታቸው አልፏል። ወረርሽኙ በተነሳበት በውሃን ቻይና የተደረገ አንድ አዲስ ጥናት፤ ተገቢውን የራስ መከላከያ ቁሳቁሶች የተጠቀሙ የጤና ባለሙያዎች ለቫይረሱ ቢጋለጡም በቫይረሱ ሳይያዙ እንደቀሩ አሳይቷል። ይህም፡ የራስ መከላከያ ቁሳቁስ አቅርቦት የጤና ባለሙያዎችን ጤንነት ከመጠበቅ አኳያ የሚጫወተውን ትልቅ ሚና ያሳየናል


የኮቪድ 19 ቫይረስ የመተንፈሻ አካላትን የሚያጠቃ እንደመሆኑ መጠን የሚተላለፈው ቫይረሱን የያዙ የውሀ እንክብሎችን ወደ መተንፈሻ አካላችን ስናስገባ ነው። በተጨማሪም እጃችን ቫይረሱ ያረፈበትን አካል ነክቶ ከሆነና ከዛም ፊታችንን ከነካን ቫይረሱ በሚዩከስ ሜምብሬን አማካኝነት ሊተላለፍ ወይም ወደ ሰውነታችን ሊገባ ይችላል። የህክምና ባለሙያዎች ለቫይረሱ ተጋላጭነት ካላቸው ሰዎች ጋር የቅርብ ግንኙነት እንዲያደርጉ ስለሚገደዱ ከሌላው ማህበረሰብ በተለየ ከእነዚህ መተላለፊያ መንገዶች ራሳቸውን መጠበቅ አለባቸው። ይህ የህክምና ባለሙያዎች ራስን መጠበቅ የሚመጣው ደግሞ N-95 ጭንብልን፣ የእጅ ጓንትን፣ የአይን መሸፈኛን፣ ፊትን የሚከልል ሽፋንን፣ ልብስንና ቆዳን የሚሸፍንን ሙሉ የሰውነት ልብስን በማድረግ እንዲሁም እነዚህን ቁሶች በተገቢው ጊዜ በመቀየር ነው


የተለያዩ ሀገራት የራስ መከላከያ ቁስ አቅርቦት እጥረት ችግርን ለመፍታትት የተለያዩ መፍትሄዎችን ሲተገብሩ ቆይተዋል። ለምሳሌ፡ ብዙ ሀገራት አለም አቀፍ የነፃ ንግድ መርህን ወደ ጎን በማድረግ የራስ መከላከያ ቁሶች ከሀገር እንዳይወጡ የሚያደርጉ ህጎችን/export ban ደንግገዋል። በብዙ የምእራባውያን አገራት N95 እንዱሁም ሰርጂካል ማስኮች ለጤና ተቋማትና ባለሙያዎች ብቻ ለሽያጭ እንዲውሉ ተደርጓል። ከሁለት የአየርላንድ ዩንቨርስቲዎች የተውጣጡ ተመራማሪዎች የራስ መከላከያ ቁሶችንን አቅራቢዎችን፣ ለጋሾችን፣ አጓጓዦችን እንዲሁም ተጠቃሚ ሆስፒታሎችን በቀላሉ የሚያገናኝ እና የራስ መከላከያ አቅርቦትን የሚከታተል CovidMedSupply የተባለ ድህረ ገፅ አቋቁመዋል። በአሜሪካ እስከ 80,000 የሚደርሱ ጭንብሎችንን በቀን ኮሎምበስ ባቴል በተባለ ሂደት ሀይድሮጅን ፐር ኦክሳይድን በመጠቀም እንዲፀዱ የሀገሪቷ የምግብና የመድሀኒት አስተዳደር ፍቃድ ሰጥቷል በሌሎች ሀገሮች የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች የውሀ እንክብልን የሚከላከሉ እንዲሁም ተደራረበው የተሰሩ ጭምብሎችን የጤና ባለሙያዎችን ታሳቢ በማድረግ እንዲያመርቱ የተደረገበትም ሁኔታ አለ። በተጨማሪም፡ በአንዳንድ ቦታዎች ግለሰቦች ያላቸውን አንድም ይሁን 10 ማስክ ባካባቢያቸው ላሉ የጤና ተቋማት ሲለግሱ ተሰተውለዋል


የኢትዮጵያ መንግስትም ወረርሽኙ መስፋፋት ከመጀመሩ በፊት ይህን በሚመለከት የተለያዩ እርምጃዎችን ወስዷል። ለምሳሌ፤ መጋቢት 18፡ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያስፈልጉ እቃዎችና ግብአቶች ወደሀገር ውስጥ ለሚያስገቡ አስመጪዎች አስፈላጊ የውጭ ምንዛሬ በቅድሚያ እንዲያገኙ ፈቅዷል። በሀዋሳ ኢንደስትሪያል ፓርክና ሌላ የኢንደስትሪያል ፓርኮች ያሉ አምራቾች፤ የመከላከያ ቁሶችን የሚያመርቱበት ሁኔታንም አመቻችቶ፤ በአሁኑ ጊዜ 14 አምራቾች ስራ ጀምረዋል። ተጨማሪ 19 አምራቾች በሳምንታት ጊዜ ውስጥ ምርት እንደሚጀምሩ፤ ምርቶቹ ለሀገር ውስጥም ለውጭ ሀገራትም ሽያጭ ላይ እንደሚውሉ ተነግሯል


ይሁን እንጂ፤ በሀገራችን የወረርሽኙን መስፋፋት ተከትሎ የጤና ባለሙያዎች ተጋላጭነት እንዲሁም፣ በቫይረሱ መያዝ በአሳሳቢ ሁኔታ እየጨመረ ይገኛል። እስካሁን በኮሮና የተያዙ የሕክምና ባለሙያዎች ቁጥር 97 ደርሷል፣ ከነዚህም ውስጥ 81 የሚሆኑት በቫይረሱ የተጠቁት ባለፉት ሁለት ሳምታት ውስጥ ነው። በተጨማሪም 2,340 የህክምና ባለሙያዎች (ካሉን ባለሙያዎች 14% የሚሆኑት) በኮሮና በሽታ ለተያዘ ሰው ተጋልጠዋል


እነዚህ ቁጥሮች አስደንጋጭ እንዲሁም በጣም አሳሳቢ ናቸው። እንደ VOA እና DW ባሉ የመገናኛ ብዙሀን እንዲሁም ‘ሀኪም’ እና ‘የኢትዮጵያ ሀኪሞች ህብረትገፆችን ጨምሮ በተለያዩ የጤና ተቋማት የሚሰሩ ብዙ የጤና ባለሙያዎቻችን በማህበራዊ ድረ ገፆች ላይ እየገጠማቸው ስላሉ የራስ መከላከያ ቁሳቁሶች እጥረትና የመገለያ ቦታዎች አለማግኘት ያለማቋረጥ አቤቱታ እያቀረቡ ይገኛሉ። ይህም ችግሩ አስቸኳይ መፍትሄን እንደሚሻ ያሳያል።


በሀገራችን ያለውን አነስተኛ የዶክተር ለታማሚ ምጣኔ ግምት ውስጥ ስናስገባ ያሉን ጥቂት የጤና ባለሙያዎች ለበሽታው ተጋላጭ መሆን እንዲሁም መታመም ይህንን የምጣኔ ቁጥር ይበልጥ እንደሚቀንሰውና የጤና አጠባበቅ ሥርዓቱ ላይ የጥራት እና የአቅም ጉድለት እንደሚያስከትል መገንዘብ ይቻላል። የዶክተር ለታማሚ ምጣኔያቸው ከሀገራችን የሚልቁ እንደ ስፔን እና ጣልያንን የመሳሰሉ አውሮፓውያን ሀገራት እንኳን የህክምና ባለሙያ እጥረት ገጥሟቸው በጡረታ ላይ ወይም በስልጠና ላይ ላሉ የህክምና ባለሙያዎቻቸው ጥሪ ሲያደርጉ አስተውለናል


የጤና ሚኒስተሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ግንቦት 24 ባወጡት መግለጫ በሚቀጥሉት አራት ወራት የጤናው ዘርፍ ወደ 130 ሚሊየን የሚጠጋ የፊት ጭምብል (mask) እንደሚያስፈልገው የተናገሩ ሲሆን፣ ወረርሽኙ ሀገራችን እንደገባ በሀገሪቷ 4 ሚሊዮን ማስክ ብቻ እንደነበረ፣ በአሁኑ ጊዜ ግን ከ7 ሚሊየን ማስክ በላይ በየተቋማቱ እንደተሰራጨ ገልፀዋል። ሚኒስተሯ ግንቦት 30 ቀን በሰጡት ገለፃቸው ደግሞ እስካሁን ሶስት ዙር ቁሶችን የማከፋፈል ስራ እንደተሰራና፣ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ለአራተኛ ዙር ማከፋፈል እየሰሩ እንደሆኑ ተናግረዋል። ሚኒስተሯ አክለውም ከኮቪድ ማእከላት በተጨማሪ ለሌሎች የጤና ተቋማት እነዚህን ቁሳቁሶች ለማከፋፈል እንደሚሰሩና የጤና ባለሙያዎችን ለመጠበቅ ተጨማሪ እርምጃዎችን እየወሰዱ እንደሆነም ገልፀዋል። እነዚህም ተቋማት በሰዎች እንዳይጨናነቁ እርምጃዎችን መውሰድ፣ የጤና ባለሙያዎችንን የመመርመር፣ አምራቾችን እና አስመጪዎች በአፋጣኝ እነዚህ ቁሶች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ የማድረግ፣ በክልሎች አማካኝነት ይደረግ የነበረውን የቁሶች ማከፋፈል በቀጥታ ወደ ተቋማት የሚደርስበትን መንገድ መዘየድ፣ በተጨማሪም እነዚህን ቁሶች ለመቆጣጠር የሚረዳ ዳሽቦርድ መስራት እንደሆኑ ዘርዝረዋልከወረርሽኙ ጅማሮ አንስቶ በአለም አቀፍ ደረጃ ያጋጠመው የራስ መከላከያ ቁሳቁስ እጥረት አሁንም ሙሉ በሙሉ አለመቀረፉ እሙን ነው። ይሁን እንጂ በሀገራችን ኢትዮጵያ ከአለም አቀፍ እንዲሁም አገር አቀፍ የቁሳቁስ እጥረት በተጨማሪ የመከላከያ ቁሳቁሶች በአግባቡ ለጤና ባለሙያዎች እንዳይዳረሱ ምክንያቶች የሆነው አንዱ ጉዳይ ወደ ሀገር ውስጥ በእርዳታ የሚገቡ ቁሳቆሶች centralized በሆነ መልኩ ተቆጥረውና ተመዝግበው፤ በግልፅ የሚታወቅ የፍላጎትና የስርጭት መመሪያን ተከትለው አለመከፋፈላቸው ነው።


TrackEthioGov/ትራክ ኢትዮ ጎቭ: ከማርች ወር ጀምሮ እያሰናዳው ባለው የልገሳ መዝገብ/ዳሽቦርድ ተመዝግበው ያሉትንና በአይነት የተለዩትን ልገሳዎች ብቻ እንኳን ብንወስድ፡ 65.55 ሚሊየን ብር የሚተመን የራስ መከላከያ ቁሳቁሶች እና የህክምና እቃዎች፣ 2 ሚሊየን ማስኮች እንዲሁም 8.7 ሚሊየንንየእጅ ጓንቶች ይገኙበታል እነዚህ ቁጥሮች ሁሉንም የህክምና ቁሳቁስ ልገሳዎች ካለማካተታቸው በተጨማሪ ሌሎች ብዙ ልገሳዎች በቁጥር ወይም በገንዘብ ሳይተመኑ ተሰጥተዋል። በልገሳ ጊዜ በቁጥር በዚህ ምህዳር ላይ የተመዘገቡ እንዲሁም ያልተመዘገቡ ልገሳዎች በምን መልኩ ተሰናድረው ለጤና ባለሙያዎች እየተከፋፈሉ እንደሆነ በቂ መረጃ የለም።በሌላ በኩል ደግሞ፣ የጤና ባለሙያዎች የራስ መከላከያ ቁሳቁስ እጥረት እንዲህ አሳሳቢ በሆነበት ጊዜ በተለያዩ እንደ ፌስ ቡክ እና ቴሌግራም የመሳሰሉ ማህበራዊ ድህረ ገፆች በብዙ መቶ ሺህ/ሚሊዮን የሚቆጠሩ ማስኮች በግል ገበያው ላይ ሲዛወሩ እናያለን። በእኛ የዳሰሳ ጥናት መሰረት፡ ከ17 በላይ የፌስቡክና ቴሌግራም ገፆች እያንዳንዳቸው በትንሹ ከአስር ሺ እስከ መቶ ሺ ማስኮችን በጅምላ ይሸጣሉ፣ አክለውም በክምችታቸው በጠቅላላ (የ17ቱ ድምር) ከ12 ሚሊየን ማስክ በላይ እንደሚገኝ ያትታሉ። እነዚህ ሽያጮች ህጋዊ ከሆኑ መንግስት እንደ አንድ ምንጭ ሊጠቀምባቸው፣ እንዲሁም ይህንን ገበያ ከግለሰቦች ግዢ ወደ ጤና ተቋማት ሊያዞር ይገባል። ነገር ግን በቅርቡ Ethiopia Check የተባለው የማህበራዊ ድረ ገፅ የእነዚህን ማስክ ሽያጮች ምንጭ ህጋዊነት ጠይቋል። በአለም ደረጃ ትልቅ እጥረት በተከሰተበት በዚህ ጊዜ በሚሊዮን የሚቆጠሩ K-N95 እና ሰርጂካል ማስኮችን ወደ ሀገር አሰገብተው የሚያከፋፍሉ ነጋዴዎች ምን አይነት ተወዳዳሪ የሆነ የግዢ ሂደትን ተጠቅመው ነው? ወይስ በተለያየ ምክንያት (በልገሳም ይሁን በመንግስት ግዥ) ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ ቁሳቁሶችን ተቀብለው በትርፍ እየሸጡ ነው የሚል ጥያቄ አንስቷል። እንደዛም ከሆነ መንግስት ይህንን ለመከላከል አስፈላጊ መዋቅሮችን በየቦታው ማስቀመጥ እና የግልፅነት ስርዓት መዘርጋት ይኖርበታል።


የመፍትሄ ሀሳቦች


ታዲያ፤ በወረርሽኙ የሚያዙና የሚሞቱ ኢትዮጵያጵያን ቁጥር እየጨመረ ባለበት ባሁኑ ጊዜ መንግስት እንዲሁም ህብረተሰቡ የጤና ባለሙያዎችን የራስ መከላከያ ቁሳቁስ እጥረት ለመቅረፍ ተጨማሪ ምን ሊያደርግ ይችላል?

 • የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ በግንቦት 30 ገለፃቸው ሊሰሯቸው እንዳቀዷቸው የዘረዘሯቸውን ዝርዝሮች ተግባራዊነት ማረጋገጥ። ተግባራዊነትን ለማረጋገጥ የአሰራርና የአተገባበር ሂደቶቹን ግልፅ ማድረግና ተጠያቂነትን የሚያበረታቱ መንገዶችን መከተል ያስፈልጋል። ግልፅ እና ተጠያቂ አሰራር ክፍተቶች እንዳይፈጠሩ እና የታቀደው እቅድ በአፋጣኝ ስራ ላይ እንዲውል ቁልፍ ሚና ይጫወታል። በጤና ሚኒስተር እቅዶች ውስጥ የተካተቱት ተግባራት የሚከተሉት ናቸው።

 • ተቋማት በሰዎች እንዳይጨናነቁ እርምጃዎችን መውሰድ

 • የጤና ባለሙያዎችንን መመርመር

 • አምራቾችን እና አስመጪዎች በአፋጣኝ እነዚህ ቁሶች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ማድረግ

 • በክልሎች አማካኝነት ይደረግ የነበረውን የቁሶች ማከፋፈል በቀጥታ ወደ ተቋማት የሚደርስበትን መንገድ መዘየድ

 • ቁሶችን ለመቆጣጠር የሚረዳ ዳሽቦርድ መስራት

 • የጤና ሚኒስትሯ ተዘጋጅቶ እንዳለቀ የተናገሩት የሀብት መከታተያ/መመዝገቢያ ዳሽቦርድ ቢያንስ ለሁሉም የህክምና ባለሙያዎች ከተቻለ ደግሞ ለህዝብ ግልፅ እንዲሆን ማድረግ እነዚህ ቁሶችች በእይታ ውስጥ ሆነው ወደ ትክክለኛ መዳረሻቸው እንዲረዱ ያግዛል ።

 • ከውጭ ሀገርም ሆነ ከሀገር ውስጥ በልገሳ የሚሰጡ ሀብቶች በቀጥታ ወደ አንድ ማከማቻ ገብተው የተዘጋጀው የሀገረ አቀፍ ፍላጎት መደብ/priority list ተከትሎ እንዲተላለፉ ማድረግ በጣም የተጠቁ ቦታዎች በአስፈላጊ ፍጥነት ቁሳቁሶቹ እንዲደርሳቸው ለማድረግ ይረዳል።

 • የራስ መከላከያ ቁሳቁስ እጥረትን ለመቀነስ በሌሎች ሀገራት እየተተገበሩ ያሉ የቴክኖሎጂ መፍትሄዎችን መከታተል እንዲሁም ሀገራዊ ተግባራዊነታቸውን መርምሮ ጥቅም ላይ ማዋል ያስፈልጋል።

 • ከመንግስት በተጨማሪ እያንዳንዱ ግለሰብ ሀላፊነት ወስዶ አስፈላጊ የራስ መከላከያ ቁሳቁሶች፤ በተለይ N-95 ጭንብሎችን፤ ለባለሙያዎች በመተው ሌሎች ጭምብሎችን ተጠቅመው ራሳቸውን መከላከልና እነዚህን ቁሳቁሶች ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ከጤና ተቋማት አውጥተው ለገበያ የሚያወርቡ ነጋዴዎችን በማጋለጥ የበኩሉን ሚና ሊጫወት ይገባል።

 • ከዚያም ባለፈ በግለሰብ ወይም በትንንሽ ኩባንያዎች ደረጃ፣ በሀገር ውስጥ ሊሰሩ የሚችሉ እንደ የፊት መከለያ ሽፋን አይነት የራስ መከላከያ ቁስን በመስራት አቅራቢያችን ላሉ የጤና ተቋማት መስጠት ይቻላል።


ለመደምደም፡ በሀገራችን የበሽታው ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ እያየለ ባለበት በአሁኑ ጊዜ፤ ለጤና ባለሙያዎችና ሌሎች የጤና ተቋማት ሰራተኞች የሚደረገው ድጋፍ ከፍተኛ ትኩረት ይሻል። በዘርፉ ያሉ ሌሎች ማነቆዎች እንዳሉ ሆነው፤ ራስን የመከላከያ ቁሳቁስ በበቂ ሁኔታ አለመቅረብ የጤና ባለሙያዎች በሙሉ አቅማቸው በሽተኞቻቸውን እንዳይረዱ ያደርጋል። ይህ ችግር በሽታዉ በሆስፒታሎች ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲሰራጭና የጤና ባለሙያዎች ስነልቦናዊ ሰላም ከመረበሽ አልፎ ቁጥራቸው እንዲቀንስ በማድረግ ወረርሽኙን ለመከላከል የምናደርገውን ሀገራዊ ፍልሚያ እንዳይፈታተን ሁላችንም የበኩላችንን ልናደርግ ይገባል።***


TrackEthioGov/ትራክ ኢትዮ ጎ የኢትዮጵያ መንግስት ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ለማገዝ የተለያዩ አካላት የሚያበረክቱትን የጥሬ እቃም ሆነ የገንዘብ ድጋፍ እየመዘገበ ለህዝብ ግልፅ በሆነ ድህረ ገፅ ያስቀምጣል። እርሱዎም ሆነ ሌላ ሰው ያበረከቱት እርዳታ ካለ በዚህ ቅፅ ብትልኩልን መረጃውን የተሙኣላ ለማድረግ ያግዘናል።

176 views0 comments